በቅንጅት አመራር አባላት በጋዜጠኞች በሲቪክ ማኅበራት ሰራተኞችና ጠቅላላው በ131 ተጠርጣሪዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ የክስ ቻርድ ለፍርድ ቤት አስገባ። የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ዐቃቤ ሕግ ተቃውሞ ያቀረበ ሲሆን ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለመመልከት የፊታችን ዕረቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ሕዳር 22 ቅ እን 1998 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት በዋለው ችሎት የቅንጅት አመራር አባላትን በተመለከተ ጠበቆች ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ ዐቃቤ ህግ መልስ ይስጥበት የተባለውን መሰረት በማድረግ ታህሳስ 7 ቀን በፅሁፍ መልስ ሰጥቷል።
ዓቃቤ ህግ የአመልካቾች የዋስ መብት ጥያቄን የተቃወመ ሲሆን አመልካቾቹ ፈጸሙት የተባለውን አመጽና አድራጎት በከባድ የወንጀል ሕግ መተላለፍ የሚያስከስሳቸው ሆኖ በመገኘቱ የ1996 ዓ.ም. የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ ውስጥ አንቀጽ ተጠቅሶ ክስ መመስረቱን እና ክሱም ለፍርድ ቤት ቀርቦ መዝገብ መከፈቱን በጽሁፍ ገልጿል።
የፌዴራል ዐቃቤ ህግ የጠቀሰው የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) (ለ)፣ 38፣ 34፣ 27(1) እና 238 (2) 258፣ 239፣ 240 (2)/ 258፣ 241፣ 237/258፣ 248/258፣ 269 ነው።
ከነዚህ ውስጥ 238(2) ወንጀሉ ሲፈፀም በሕዝብ ደህንነት ወይም ኑሮ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ደርሶ እንደሆነ፣ አድራጊው በዕድሜ ልክ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል ይላል።
አንቀጽ 258 ከባድ ሁኔታ በሚል የተቀመጠ ሲሆን በዚህ ምዕራፍ ወንጀል በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት እንደሚያስቀጣ ሕጉ በደነገገባቸው ሁኔታዎች ሁሉ ፍርድ ቤቱ የሞት ቅጣት የሚወስነው ተከሳሹ ከአንድ እስከ አራት የተዘረዘሩትን ፈጽሞ ሲገኝ ነው።
ከነዚህም ውስጥ አድራጎቶቹ የታቀዱትና የተፈጸሙት ከአድማ የተነሳ እንደሆነ ወይም የጦር መሳሪያ በያዙ ክፍሎች እንደሆነ ወይም ወንጀለኛው ከውጭ አገር ወይም ከውጭ መንግስት የፖለቲካ ወይም ሌላ ድርጅት ባገኘው ሀብት የጦር መሳሪያ ወይም በማናቸውም እንኳን በሚያገኘው እርዳታ ወይም ድጋፍ ወንጀሉን ፈጽሞ እንደሆነ ወይም በቦንብ፣ በድማሚት ወይም በሌላ በማናቸውም በሚፈነዳ መሣሪያ ወይም በብዙ ሰው ላይ አደጋ ሊደርስ በሚችል ይህንኑ በመሰለ የማሸበሪያ መሣሪያ ወይም ዘዴ ወንጀሉን ሰርቶት እንደሆነ ነው።
ዐቃቤ ሕግ በዚሁ መሰረት የአመልካቾች የዋስ መብት ጥያቄ የተነሳው በምርመራ መዝገቡ ላይ የዐቃቤ ሕግ ውሳኔ ከመታወቁ በፊት በመሆኑ እና ውሳኔ ታውቆ ክሱ ለፍርድ ቤት የቀረበ በመሆኑ አሁን የቀረበው የዋስ መብት ጥያቄ ታልፎ በመደበኛ የክሱ ሂደት ሊታይ ይገባል እንዲባልለት ጠይቋል።
ፍ/ቤት ከላይ የተጠቀሰውን የሚያልፈው ሆኖ ከተገኘ ተከሳሾቹ የተመሰረተባቸው ክስ ወደፊት የጥፋተኝነት ውሳኔ የሚያሰጣቸው ሆኖ ከተገኘ ከ15 ዓመት በላይ በማለትም በዕድሜ ልክና በሞት የሚያስቀጣ ከመሆኑም በላይ በፈጸሙት ወንጀል በበርካታ የሰው ህይወትና አካል እንዲሁም በሕዝብና በመንግስት ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ውጤት በመሆኑ በ/መ/ሕ/ሥ/ሥ ቁጥር 63(1) መሰረት፤
በተጨማሪም ተከሳሾቹ ከእስር ቢለቀቁም ቀደም ብሎ የፈጸሙዋቸውን የወንጀል ተግባሮች እና አመጽን ሊቀጥሉበት ይችላሉ የሚል ግንዛቤ ሊወስድ የሚያስችል በቂ ሁኔታ ስለመኖሩ ጠቅሶ በዋስ ቢለቀቁም ግዴታቸውን አክብረው በቀጠሮው ይቀርባሉ ተብሎ ስለማይገመትና እና በዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎች አንጻርም የሚያሳድረው ተጽእኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ወ/መ/ሕ/ሥ/ቁጥር 67 (ሀ/ለ/ሐ) መሰረት፤
አመልካቾች የዋስ መብታቸው ለማስጠበቅ የሚጠቅሱት አንቀጽ 19(6) በሕግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍ/ቤት የተከሳሾቹን የዋስ መብት ጥያቄ ላለመቀበል ጭምር የሚያስችል መሆኑን ሁሉ በማገናዘብ እና ከዚህ በላይ በተጠቀሱት የወ/መ/ሕ/ሥ/ ሕጎች መሰረት የተከሳሾች የዋስ መብት ጥያቄ ውድቅ እንዲሆንላቸው ጠይቀዋል።
የአመልካቾች ጠበቆች የዓቃቤ ሕግ መልስ ከተነበበ በኋላ ፖሊስ የእስር ክትትልን በተመለከተ እና የክስ ቻርጅን እየተመለከተ እያለ በሚያቀርበው ሁለት መንገድ እየተጫወተ ነው ያለው ሲሉ ተከራክረዋል።
ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን በተመለከተ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያቀረቡት አቤቱታ እና በዓቃቤ ሕግ የቀረበውን መቃወሚያ አይቶ ዕረቡ ታህሳስ 12 ቀን ቀጥሯል።
በዕለቱ ዓቃቤ ሕግ በ131 ግለሰቦች ላይ ያስገባው የክስ ቻርጅ በተመሳሳይ ዕለት ለተከሳሾቹ ደርሷቸው እንዲያዩት እና መልስ ለመስጠት የሚያስፈልጋቸው ቀናትም እዛው እንዲወሰን ተብሏል።